የዘረኛነት ወረርሽ
ሰሞኑን አንድ የንግድ ተቋማት ማስተዋወቂያ ቡክሌት ደርሶኝ ተገርሜ እያየሁት ነው፡፡መጽሔቱ ክርስቲያን ነጋዴዎችን የያዘ መሆኑን ገና ከመግቢያው ይገልጣል፡፡ ክርስቲያኖችእርስ በርሳቸው ሊረዳዱ እንደሚገባ፣ የጌታ ልጆች በአንድነት መኖር እንዳለባቸው፣ከዚያም አልፎ አንዱ ከሌላው በመግዛት ወይንም በመጠቀም ወንድማማችነትንእንዲያሰፍኑ፣ ያም ለምድሪቱ በረከት መሆኑን በጥቅስ እያዋዛ ይገልጣል፡፡
እየገረመኝም እየደነገጥኩም ነበር ያነበብኩት፡፡ በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዘረኛነትይህንን ያህል ሥር ሰድዷል ማለት ነው? አልኩ ለራሴ፡፡ ለመሆኑ ይህቺ ሀገር በስንትዓይነት ዘረኛነት እንድትሰቃይ ይሆን የተፈረደባት? ስልም ጠየቅኩ፡፡ ዛሬ በዚያች ሀገር«ገንዘባችን በየክልላችን» ብቻ ሳይሆን በየቋንቋችንም በመግባት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያየሚለው እየቀረ የኦሮምያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የሶማልያ ባንኮች ብቅ ብቅእያሉ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ደግሞ በይፋ ስማቸውን ባይገልጡም በአንድ እምነት ሥርያሉ ሰዎችን ብቻ በአክስዮን የሚያሰባስቡ ባንኮችም እየታዩ ነው፡፡
ዘረኛነት ማለት እንዴው በቀላሉ ሲገለጥ አንድን ሰው በዕውቀቱ፣ በችሎታው፣በዐቅሙ፣ በትምህርት ደረጃው ወይንም በሌላ መለኪያ ሳይሆን በወገንተኛነቱ ብቻመመዘን ማለት ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ወገንተኛነትን ከሌሎች መለኪያዎች ሁሉ አልቆመመልከት ማለትም ይሆናል፡፡
ሀገርሽ ወዴት ነው ብዬ ብጠይቃት
ከም ከም ብላ ሳቀች ነገሩ ቢደንቃት አይደለ ብሂሉ
ዘረኛነት ለአንዲት ሀገር በሽታዋ ሲሆን ነገሮችን ሁሉ በግለሰባዊነት ወይንም ደግሞበጋራ ጥቅሞች እና አስተሳሰቦች ሳይሆን በአንዳች የቡድን መልክ ብቻ ማየትይጀመራል፡፡ ዘረኛነት በመወለድ እና በክልል፣ በጎሳ እና በሀገር ልጅነት ብቻ የሚከሰትአይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ መልከ ብዙ ገጽታ ነው ያለው፡፡ የጎሳ፣ የፓርቲ፣ የሃይማኖት፣የማኅበር፣ የሠፈር፣ ወዘተ ዓይነት ዘረኛነቶች አሉ፡፡
የጎሳውን ዓይነት ዘረኛነት በውጭም በውስጥም ያለን የዚህች ሀገር ሰዎች ጠግበነዋል፡፡የት ተማርክ? ከሚለው ይልቅ የት ተወለድክ? የሚለው ጥያቄ አሰልችቶናል፡፡ ምንትችላለህ ሳይሆን ምን ትናገራለህ? ሆኗል መመዘኛችን፡፡ አንድ ሰው የእገሌ ጎሳ አባልበመሆኑ ምክንያት ይወደዳል፣ ይጠላል፡፡ ይከበራል፣ ይናቃል፡፡ ሥራ ያገኛል፣ ሥራያጣል፡፡ ይኮራል፣ አንገት ይደፋል፡፡ ዕድል ይከፈትለታል፣ ዕድል ይዘጋበታል፡፡ ይሾማል፣ይሻራል፡፡
ሳቅና ጨዋታ ዝና ካማራችሁ
እንደኛ እንትን ላይ በተወለዳችሁ
የሚለው ዘፈናችንኮ ጤነኛ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳቅ፣ ጨዋታ እና ዝናን ለማግኘትአትችሉም እያለን ነው፡፡ ለምን ብንለው ከኛ ሀገር አልተወለዳችሁማ፤ ምን አማራጭአለን፡፡ መልሰን አንወለድ፡፡
ሌላ ቋንቋ ሲሰሙ ጆሯቸውን የሚያሳክካቸው፤ ፊታቸው የሚለዋወጥ፣ ንዴት ንዴት የሚላቸውእንዳሉ ሁሉ፤ ያንን ቋንቋ ሲሰሙ ቸርነታቸው ሁሉ የሚከፈት፣ መስተንግዷቸው የሚሟሟቅ፣አድሏዊነታቸው የሚጨምርም አሉ፡፡
የጎሳ ዘረኛነት ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ እና ለማግባባት ከምንሠራው ሥራይልቅ ልዩነታቸው እንዲገባቸው የምንሠራው ሥራ ይበልጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያን በመሰለችብዙ ቋንቋዎች በሚነገርባት ሀገር አንድ ተማሪ ከሥራ ቋንቋ ውጭ የራሱን አካባቢ ቋንቋ ብቻነው የሚማረው፡፡ ከዚያ ውጭ የሚማረው እንግሊዝኛ ነው፡፡ ከአካባቢው ቋንቋ ውጭ ያለውንየሚያስተምሩት መምህራንም አንዳንድ ጊዜ የጠላት ሀገር ቋንቋ የሚያስተምሩ ይመስል ወይ እነርሱ በግዴለሽነት ያስተምራሉ አለያም አካባቢያቸው በንቀት ያያቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሕዝብ የሚናገራቸው ቋንቋዎች አሉ፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ሶማልኛን የመሰሉ፡፡ አንድ ተማሪ ከአካባቢው ቋንቋ በተጨማሪ ቢቻል ሌሎች ሁለትካልተቻለም አንድ የሌላ አካባቢ ቋንቋ መርጦ እንዲማር ቢደረግ እንዴት መልካም ነበር፡፡በመጀመርያ ደረጃ ጥላቻውን ያስቀረዋል፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር የመጥላት ሁኔታው ዝቅተኛነውና፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ያግባባናል፡፡ አንዳንዴኮ ከተወለድንበት እና ካደግንበት ክልል ውጭመሄድ ውጭ ሀገር እንደመሄድ እየሆነብን ነው?
አንድ የሶማሌ ሰው (6.0% ተናጋሪ አለው) አማርኛ (32.7% ተናጋሪ አለው) እናኦሮምኛ (31.6% ተናጋሪ አለው) ቢችል ከስድሳ በመቶ በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያሕዝብ ጋር ይግባባል ማለት ነው፡፡ ይህም አንዱ ወደ ሌላው ሄዶ የመሥራት፣ ተጋብቶእና ተዋልዶ የመኖር ብሎም ከሌላው ወገኑ ጋር ልብ ለልብ የመግባባት ዕድሉንይጨምረዋል፡፡ እንግሊዝኛ በትምህርት ቤቶቻችን ያለውን ክብር ግማሽ ያህል የሀገራችንሌሎች ቋንቋዎች የላቸውም፡፡
ይህንን አመለካከት ቀርፈው ሕዝቡን ልዩነት ወደሚከበርበት አንድነት ያመጡታልየሚባሉት የፖለቲካ ልሂቃንም ራሳቸው ዘውገኞች ሆነዋል፡፡ አብዛኞቹ ፓርቲዎቻችንጎሳን ወይንም አካባቢን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ያንን ፓርቲ በአሠራሩ፣ በአመለካከቱእና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ብትወዱት እንኳን እንደገና እዚያ ክልል ገብታችሁ ለመወለድባለመቻላችሁ ብቻ ከአባልነት ትታቀባላችሁ፡፡
የሀገሬ ሰው «መወለድ ቋንቋ ነው» የሚለው እዚህ ላይ አይሠራም፡፡ መወለድ እኛ ሀገርቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ፓርቲም፣ ሥራም፣ ሹመትም፣ ገንዘብም፣ መሬትም፣ ርእዮተዓለምም ጭምር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አንድን ወገን ነጻ የሚያወጡ አያሌ ድርጅቶችአሉን በሀገራችን፡፡ ማን ማንን ከማን ይሆን ነጻ የሚያወጣው? አማራው ከትግሬው፣ትግሬው ከአማራው፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ አማራው ከኦሮሞው ነው ነጻ የሚወጣው?እየተጨቋቆንን ነው የምንኖረው ማለት ነው?
አንዳንዶቹ ፓርቲዎች እኛ ሕዝቡን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነው ነጻ የምናወጣውይላሉ፡፡ መቼም ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ መውጣትን የሚጠላ የለም፡፡ ግንከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ ለመውጣት የግድ ነጻ አውጭ ፓርቲ ያስፈልገናል?በዓለም ላይ ራሳቸውን ከድህነት አረንቋ ያወጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በነጻአውጭ ፓርቲዎች ነው እንዴ ነጻ የወጡት?
ፓርቲዎቻችን የጎሳ ዘረኛነትን ብቻ አይደለም የፓርቲ ዘረኛነትንም መላቀቅ አልቻሉም፡፡ከራሴ ፓርቲ አባል ውጭ ያለው ሁሉ ስሑት፣ ፀረ ልማት፣ ጨቋኝ፣ አንድነትንየሚያናጋ፣ አገር አጥፊ፣ ጠላት፣ ከሀዲ፣ ለሀገር የማይጠቅም ነው ብሎ ማሰብ ነውየፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ ብቻ ማድነቅ፣ መውደድ፣ መሾም እናማግነን ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ መጥላት፣ ማነወር፣ ማራቅ እናማግለል ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡
በርግጥ በአሁኑ ጊዜ በሕዝባችን ዘንድ ሰውን ብቻውን ማየት ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ሰው በቡድን ውስጥ ነው የሚታሰበው፡፡ በፓርቲው፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣ በክልሉ፣በሚኖርበት አካባቢ፣ በሥራ ዓይነቱ፣ ነው የሚታየው፡፡ እገሌ ሳይሆን እነ እገሌየሚለው ድምፅ ነው የሚሰማው፡፡
ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊውን የሚሰብኩት፣ ፍቅር እና ሰላም ዋና አጀንዳዎቻቸውየሆኑት የእምነት ተቋማት እንኳን ሳይቀሩ በዘረኛነት አረንቋ ውስጥ ሰምጠውበታል፡፡በአንድ በኩል የእምነት ዘረኛነት በሌላ በኩል ደግሞ የጎሳ ዘረኛነት እያላጋቸው ነው፡፡
አንድ ሰው በንግዱ፣ በአገልግሎቱ እና በሞያው መመረጥ ያለበት ባለው ችሎታ፣ ዐቅምእና ጥራት መሆን ነበረበት፡፡ አሁን አሁን ግን የኛው እምነት ሰው መሆኑ የበለጠ ቦታእየተሰጠው መጥቷል፡፡ ሙስሊሙ ሙስሊሙን ነጋዴ፣ ክርስቲያኑም ክርስቲያኑን ነጋዴእንዲመርጡ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች እየወጡ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው የንግድ እናየአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በሃይማኖታቸው ዘውግ ብቻ ከፍለው ከእነዚህ ብትገዛይመረጣል እያሉን ነው፡፡ ገንዘባችን በየእምነታችን እንዲሆን እየተሰበክን ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ ጥራቱ እንዴት ነው? የሚለው ቀርቶ ሙስሊም ነው የከፈተው ወይስክርስቲያን? ኦርቶዶክስ ነው የከፈተው ወይስ ፕሮቴስታንት ሆኗል ጥያቄው፡፡ መርፌውንበየእምነታችን ሊወጉን የተዘጋጁ የሕክምና ተቋማትም ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በአንዳንድመሥሪያ ቤቶች ለመቀጠር የአንድ እምነት ተከታይ መሆን ብቻ ከትምህርትም፣ከልምድም በላይ ዋጋ ሲኖረው እያየን ከመገረም አልፈን ለምደነዋል፡፡
የእምነት ተቋማቱ ከዚህም አልፈው የጎሳውን ዘረኛነት የሚያባብሱ ተቋማትም ሆነዋል፡፡ጎጃሜ ጎጃሜውን፣ ጎንደሬ ጎንደሬውን፣ ትግሬ፣ ትግሬውን፤ ኦሮሞ ኦሮሞውን፣ ወሎወሎዬውን ሲስበው ማየት ለተቋማቱ ቅርብ ለሆነው ብቻ ሳይሆን ርቆ ላለውምእመናቸውም የዕለት ዜና ሆኖለታል፡፡ የአንደኛው ወገን በእምነት ተቋማቱ የሥልጣንእርከን በወጣ ቁጥር፣ የእምነቱን ተከታዮች ከማብዛት ይልቅ የወንዙን ልጆች ማብዛትዋናው ተልዕኮው እየሆነ ነው፡፡
መካ ላይ አላሁ አኩበር ያለው ቢላል ኢትዮጵያዊ እንጂ ሳዑዲያዊ አለመሆኑ ተረስቷል፡፡ደብረ ዳሞ ላይ የሚከብሩት አቡነ አረጋዊ የአውሮፓ ሰው እንጂ ኢትዮጵያዊእንዳልነበሩ ተዘንግተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብለውየሚያስተናግዱበት፣ በእምነቱ ከመሰላቸው ሀገራቸውን ሀገሩ አድርገው የሚሰጡበት ዘመንእንዳይቀር ያሰጋል፡፡
ስንቶች ከሌላ ክልል ብቻ ሳይሆን ከሌላ ሀገር መጥተው፣ ትውልዳቸውንም ረስተውኢትዮጵያውያን ሆነው ቀርተዋል፡፡ «እኔስ በሀገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ» ነበርየምንለው፡፡ ዛሬ ይሄ ተረት ሊሆን ነው መሰለኝ፡፡ አቡነ አረጋዊን ትግሬ፣ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስንም አማራ አድርጎ የሚያይ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ሁለቱም ግን እንኳንእና ትግሬ እና አማራ ኢትዮጵያዊም አይደሉ፡፡
ልጁ ሊቀጠር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል፡፡ ታድያ መካሪዎች «ስትሄድ ጳጳሱየሀገራቸውን ሰው ይቀጥራሉና ሀገርህ የት ነው ካሉህ ያንተን አትናገር የርሳቸውን ሀገርተናገር» ብለው ይነግሩታል፡፡ ታድያ ጳጳሱ ፊት ሲቀርብ የሀገራቸው ስም ጠፋው አሉ፡፡
እንደገባ ያ የተነገረው አልቀረም
«ሀገርህ የት ነው?» አሉት
«የርስዎ ሀገር» አላቸው፡፡
«የኔ ሀገር የት ነው?» አሉት
«ከኔ ሀገር» አላቸው አሉ፡፡ ምን ያድርገው፡፡
አንዳንዶችማ ከዚህም ወርደው ወርደው የቆብ ዘረኛነትም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሕጋውያንካህናት ከታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪነት እንዲወገዱ ዐዋጅ ያወጣው ማን ይሆን? ዛሬለሹመት ዋና መመዘኛው መመንኮስ ሆነና «መነኮሰ ሞተ» የሚለው ትርጓሜ «መነኮሰበላ» ወደሚለው ዞረ፡፡ በዚህ የቆብ ዘረኛነት ምክንያትም መመንኮስ የሌለባቸው ለሥራእና ለሹመት ሲሉ እንዲመነኩሱ አንዳንዶችም ሚስቶቻቸውን ደብቀው እንዲመነኩሱአደረግናቸው፡፡ በተለይም የውጩ ሀገር ዕድል ሁሉ ከሕጋውያን ይልቅ ለመነኮሳቱ እጅግክፍት እየሆነ ሲመጣ፣ ያልገባቸው እና ያልተገባቸው መነኮሳት እየበዙ መጡ፡፡
ከዚህም አልፎ ምንኩስናዊ ሕይወቱ ሳይሆን የት መነኮሰ? የሚለው የዘረኛነት መለኪያእየሆነ ነው፡፡ እናም የት ብመነኩስ የምንኩስናን ተጋድሎ እፈጽማለሁ? መባሉ ቀርቶየት ብመነኩስ ቶሎ ሹመት አገኛለሁ? ሆነ ጥያቄው፡፡
«የኛ ልጆች» የሚሉ የማኅበርተኞችን የዘረኛነት ቋንቋስ ሰምታችሁ አታውቁም፡፡ ዛሬ ዛሬአያሌ ማኅበራት እየተፈጠሩ ነው፡፡ የሃይማኖት፣ የጉዞ፣ የሞያ፣ የበጎ አድራጎት፣ የክብካቤ፣የሌሎችም ማኅበራት፡፡ አንድን ሥራ ለማከናወን አንድነት መፍጠሩ መልካም ሆኖ ሳለዘረኛነቱ ግን ከፋ፡፡ «እንዲህ ሲል ያውካል» አለ ተርጓሚ፡፡ የሰውን ስሕተተኛነት እናትክክለኛነት ከማኅበራቸው አባልነት አንፃር ብቻ የሚተነትኑ ማኅበርተኞች አሉ፡፡
ይህን የመሰለ ቁመና ይዘሽ
ምናለ ፈጣሪ የኛ ባረገሽ
የሚለው ሀገርኛ ዘፈን ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡
ምን መልካም ብትሠሩ፣ ምን ተአምር ብትፈጽሙ እነርሱ ከገቡበት ካልገባችሁ ሥራችሁሁሉ የመርገም ጨርቅ ይሆናል፡፡ ምን ተሠራ? ሳይሆን ማን ሠራው? ነው ለእነርሱቁም ነገሩ፡፡ በማኅበር ይወዳሉ፣ በማኅበር ይጠላሉ፣ በማኅበር ያቀርባሉ፣ በማኅበርያገላሉ፣ በማኅበር ያጸድቃሉ፣ በማኅበር ይኮንናሉ፣ በማኅበር ይረዳሉ፣ በማኅበርይነፍጋሉ፡፡ አባል ከሆናችሁ ሁለት እና ሁለት አምስት ይሆንላችኋል፤ አባል ካልሆናችሁግን እንኳን አምስት አራት አይሆንላችሁም፡፡
በጎ ነገር ስትሠሩ ካዩዋችሁ ሊያበረታቷችሁ እና ሊያግዟችሁ አይደለም የሚፈልጉት፤ሊያደንቋችሁ እና ሊያመሰግኗችሁ አይደለም የሚተጉት፤ አባል ሊያደርጓችሁ እንጂ፡፡ምክንያቱም ከማኅበራቸው ውጭ በጎ ነገር ሲሠራ ማየት ስለማይፈልጉ፡፡
ዘረኛነት የሁላችንም ጠባይ እየሆነ ነው፡፡ ከጎሳው ብናመልጥ፣ ከፓርቲው፣ ከፓርቲውብናመልጥ ከእምነቱ፣ ከእምነቱ ብናመልጥ ከማኅበሩ ጎጠኛነት ውስጥ መገኘታችንአልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ ሰዎች በሥራቸው፣ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በችሎታቸው፣በዐቅማቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በትጋታቸው እና በጥረታቸው ሳይሆን በአንዳችወገንተኛነታቸው እንዲመዘኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ወልጋዳ ሚዛን ደግሞ ወዳጆችንእንጂ ጎበዞችን፣ ወገንተኞችን እንጂ ሊቆችን ዕድል አይሰጥም፡፡
አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆችእንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህልተሰባስበን አልነበር?
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! አሜን።
የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
ReplyDeleteእነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.