By Tade Tekle · Wednesday, October 19, 2010
ጽጌ የሚለው ቃል የግዕዝ ሲሆን አበባ የሚል የአማርኛ ፍቺ ይሰጠናል፡፡ ከመስከረም ፳6 እስከ ሕዳር 6 ድረስ ያለው ወቅት “ወርሃ ጽጌ” የሚባል ሲሆን ስያሜው በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የክረምቱ ጨለማ ተገፎ ብርሃን የሚፈነጥቅበት፤ አበቦች ለዓይን ማራኪ የሆነውን ሰሎሞን እንኳን በክብሩና በጥበቡ ሊለብሰው ያልተቻለውን በእደ ሰብእ ያልተዘጋጀውን ውብ የሆነ ልብሳቸውን ተጎናጽፈው የሚመለከታቸውን ሁሉ ትኩረት የሚስቡበት፤ ለአፍንጫ ተስማሚ የሆነውን ጥዑም መዓዛቸውንም እንካችሁ ብለው ያለስስት የሚቸሩበት፤ አእዋፍ ዝማሬያቸውን ከወትሮው በላቀ ሁናቴ ለጆሮአትን የሚያንቆረቁሩበት ንቦች ከአበባ አበባ እየዘለሉ ጣፋጭ ማርን የሚያዘጋጁበት ሁሉ አምሮ ሁሉ ደምቆ አዲስ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፤ ይህን ጊዜ ወርሃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ ተብሎ መሰየሙን ልብ ይሏል፡፡
“አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።” ሉቃ 12፥27
በዚህ ወቅት ባሉት አርባ ዕለታት በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን አንድ ትልቅ ጉዳም ይታሰባል፡፡ የእመቤታችን ስደት፡፡
“እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው።” እንዲል ማቴ 2፥13
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያዊው ሊቅ የአባ ጽጌድንግል ውብ ድርሰት የሆኑት “ማኅሌተ ጽጌ” እና “ሰቆቃወ ድንግል” የተሰኙት የእመቤታችንን የስደት ጉዞ የሚያስቃኙ ዝማሬዎች በሊቃውንት አባቶች፣ በአባቶች እናቶችና ወጣቶች ሲዘመትር ይታራል፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ከእመቤታችን ስደት በረከትን ያገኙ ዘንድ “ጾመ ጽጌ፣ የጽጌ ጾምን” በፈቃዳቸው የጾሙታል፡፡
እኛም ከሃገር ለሃገር ያለ ረዳት ዘመድ አንድ ልጇን መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ የተንከራተተችውን እመቤት እናስብ ዘንድ አበው በማኅሌት ሲዘምሩ ከሚያደርሱት አርኬ፣ ከሚወርቡት ወረብና ከሚመረግዱት ዚቅ በጥቂቱ በተከታታይ ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡ ለዛሬው እነሆ፡፡
በመጀመሪያው እሁድ የሚጸነጸል አርኬ
ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ እምአፅሙ፡፡ጽጌ ለገብርኤል ምስለ ሰላሙ፡፡ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዐዛ ጣዕሙ፡፡ለተአምርኪ አኃሊ እሙ፡፡ማኅሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ
በመጀመሪያው እሁድ የመጀመሪያው ዓቢይ ወረብ
ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ እም አፅሙ ለዘአምኃኪ ጽጌ ለገብርኤል ምስለ (በይነ) ሰላሙ (2)ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዐዛ ጣዕሙ(2)
ከማኅሌቱ በረከት ያገኙ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡
ከእመቤታችን በረከት ይክፈለን የምግባረ ሰናይ የተሰደድነውንም ወደ ሰማያዊት ሃገር ወደ ሆነም በጎ ምግባር ይመልሰን አሜን፡፡


No comments:
Post a Comment