Pages

Monday, October 17, 2011

ዘመነ ጽጌ {በዲያቆን መልአኩ እዘዘው የኔነህ}


«ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ ፤
ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፤
ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ››
ቅዳሴ ማርያም


ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡
በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። ምእመናን ቤተክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት በፍቅርና በደስታ ይዘክሩታል ፡፡ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማግኘት በርካታ ክርስቲያኖች የአዋጅ ጾም ባይሆንም በፈቃደኝነት ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡
የእመቤታችን ስደት የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ስደት ነው፡፡ ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፈው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ሰብአ ሰገል «የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናል» እያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡» ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ /በአማካሪዎቹ ግፊት ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት የሚሆን ዕድሜ ያላቸውን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. 1.13-18
«እነርሱም(ሰብአ ሰገል ) ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13 14/እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሔደ፡፡ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያ ኖረ፡፡ /ማቴ 2-13-15/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ፤ ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡
እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡
በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳድደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስደታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥተው ሀገራችንን ባርከዋል።
ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/፡፡

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን «.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..» የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡በኋላ በዚህች ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን በእመቤታችን ስም ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን ተከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ /384-412 ዓ.ም/ ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል ፡፡
ነቢያት ስለጌታ ትንቢት በመናገራቸው፣ እመቤታችን የጌታ እናት በመሆኗ፣ ሐዋርያት ስለጌታ በማስተማራቸው ተሰደዋል፡፡የጌታ አገልጋይም እናትም የሆነችው የእመቤታችን ስደት ግን. . . ከሁሉ የሚለይ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት ልዩ የሚያደርገው: -

1. ሕግን በመተላለፉ ከገነት ተሰዶ የነበረውን አዳምን ለመካስ የተደረገ በመሆኑ
2. በግብጽ ነግሦ የነበረውን አምልኮት ጣኦት ለማሳደድ የተደረገ ስለሆነ የጌታችንና የእናቱ ስደት ልዩ ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ግብጽ ስትሰደድ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር አግኝቷታል፡፡ እሾህ እየወጋት እንቅፋት እየመታት ተጉዛለች /ተሰዳለች/፤ በስደቷም ረሃብና ጥም፣ ችግርና መከራ ደርሶባታል፡፡ በበረሃው ወንበዴዎችን ባየች ጊዜም በስደት ከሄሮድስ ጭካኔ ከሀገር ያወጣሁትን ልጄን ይገድልብኛል ብላ መሪር እንባ አልቅሳለች፡፡በስደቷ ወቅት በደረሰባት ረሐብና ጥም የተነሣ ወደ መንደር ገብታ ብትለምን በችግር ምክንያት የሰው ፊት ማየት ከእሳት የበለጠ ወላፈኑ ስለሚያቃጥል የሰው ፊት ገርፏታል፡፡ የትእማን ቤተሰቦች ዘብተውባታል፡፡
«ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሸክማችንን ሊሸከም ነውና ውኃውን ለፍጥረታት የሚሰጥ እርሱ እየጠማው፤ እንስሳትን የሚመግብ እየራበው ምድርን በልምላሜ የሚያለብስ ተራቁቶ ፣የኛን ከገነት መሰደድ የመጣብንን ዕዳ ሊክስልን ከእናቱ ጋር ተሰደደ፤ ድንግል ማርያምም የአምላክ እናት ሆና መከራን ቀመሰች፡፡ ጌታን አዝላ በረሐብ አለንጋ ተገረፈች፡፡
በመጨረሻ ግን ያ ሁሉ የመከራና የስቃይ ስደት ሲያበቃ «አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ» ሲል በመኃልየ ማኀልይ ዘሰሎሞን ተነግሮ የነበረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከዚያ ሁሉ መከራና ስደት በኋላ ልጇን ይዛ ወደ ናዝሬት ተመልሳለች፡፡
የእመቤታችንን ስደት ስናስብ «ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲነግሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» /ማቴ 5-11/ የሚለውን የስደት ዋጋ ጭምር እያሰብን መሆን ይገባል፡፡
ይህንንም የእመቤታችንን ስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ በማኅሌትና በመዝሙር ትዘክራለች፡፡ ካህናቱም በዕለተ ሰንበት ከምሽት ጀምረው በማኅሌትና በመዝሙር ምስለ ፍቁር ወልዳን /የልጇ እና የእርሷ/ ሥዕል ይዘው ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡
ይህም የእመቤታችንን ስደት ለማጠየቅ ነው፡፡ ሌሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰባቸውን መከራ ለማስታወስ የፍቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡
እኛ ክርስቲያኖች በቅድስት ቤተክርስቲያን ተገኝተን በመንፈስ የሩቁን አቅርበን የእመቤታችንን ስደት በእምነት እያየን በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታችን በዜማ «መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ንጹሕ፣ ፀአዳ ፣ቀይህና ብሩህ የሚሆን ልጅሽን ታቅፈሽ ርኅሩኅ የሆነ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትለሽ ከሐዘናችንና ከችግራችን ታረጋጊን ዘንድ ፈጥነሽ ድረሽልን» ልንላት ያስፈልጋል፡፡
በቅዳሴያችንም «ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ እንላለን፡፡

«ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ
ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ ፤
ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ››
ቅዳሴ ማርያም
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! አሜን።

የዘረኛነት ወረርሽ


ሰሞኑን አንድ የንግድ ተቋማት ማስተዋወቂያ ቡክሌት ደርሶኝ ተገርሜ እያየሁት ነው፡፡መጽሔቱ ክርስቲያን ነጋዴዎችን የያዘ መሆኑን ገና ከመግቢያው ይገልጣል፡፡ ክርስቲያኖችእርስ በርሳቸው ሊረዳዱ እንደሚገባ፣ የጌታ ልጆች በአንድነት መኖር እንዳለባቸው፣ከዚያም አልፎ አንዱ ከሌላው በመግዛት ወይንም በመጠቀም ወንድማማችነትንእንዲያሰፍኑ፣ ያም ለምድሪቱ በረከት መሆኑን በጥቅስ እያዋዛ ይገልጣል፡፡
እየገረመኝም እየደነገጥኩም ነበር ያነበብኩት፡፡ በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዘረኛነትይህንን ያህል ሥር ሰድዷል ማለት ነው? አልኩ ለራሴ፡፡ ለመሆኑ ይህቺ ሀገር በስንትዓይነት ዘረኛነት እንድትሰቃይ ይሆን የተፈረደባት? ስልም ጠየቅኩ፡፡ ዛሬ በዚያች ሀገር«ገንዘባችን በየክልላችን» ብቻ ሳይሆን በየቋንቋችንም በመግባት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያየሚለው እየቀረ የኦሮምያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የሶማልያ ባንኮች ብቅ ብቅእያሉ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ደግሞ በይፋ ስማቸውን ባይገልጡም በአንድ እምነት ሥርያሉ ሰዎችን ብቻ በአክስዮን የሚያሰባስቡ ባንኮችም እየታዩ ነው፡፡
 ዘረኛነት ማለት እንዴው በቀላሉ ሲገለጥ አንድን ሰው በዕውቀቱ፣ በችሎታው፣በዐቅሙ፣ በትምህርት ደረጃው ወይንም በሌላ መለኪያ ሳይሆን በወገንተኛነቱ ብቻመመዘን ማለት ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ወገንተኛነትን ከሌሎች መለኪያዎች ሁሉ አልቆመመልከት ማለትም ይሆናል፡፡
ሀገርሽ ወዴት ነው ብዬ ብጠይቃት
ከም ከም ብላ ሳቀች ነገሩ ቢደንቃት አይደለ ብሂሉ
ዘረኛነት ለአንዲት ሀገር በሽታዋ ሲሆን ነገሮችን ሁሉ በግለሰባዊነት ወይንም ደግሞበጋራ ጥቅሞች እና አስተሳሰቦች ሳይሆን በአንዳች የቡድን መልክ ብቻ ማየትይጀመራል፡፡ ዘረኛነት በመወለድ እና በክልል፣ በጎሳ እና በሀገር ልጅነት ብቻ የሚከሰትአይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ መልከ ብዙ ገጽታ ነው ያለው፡፡ የጎሳ፣ የፓርቲ፣ የሃይማኖት፣የማኅበር፣ የሠፈር፣ ወዘተ ዓይነት ዘረኛነቶች አሉ፡፡
የጎሳውን ዓይነት ዘረኛነት በውጭም በውስጥም ያለን የዚህች ሀገር ሰዎች ጠግበነዋል፡፡የት ተማርክ? ከሚለው ይልቅ የት ተወለድክ? የሚለው ጥያቄ አሰልችቶናል፡፡ ምንትችላለህ ሳይሆን ምን ትናገራለህ? ሆኗል መመዘኛችን፡፡ አንድ ሰው የእገሌ ጎሳ አባልበመሆኑ ምክንያት ይወደዳል፣ ይጠላል፡፡ ይከበራል፣ ይናቃል፡፡ ሥራ ያገኛል፣ ሥራያጣል፡፡ ይኮራል፣ አንገት ይደፋል፡፡ ዕድል ይከፈትለታል፣ ዕድል ይዘጋበታል፡፡ ይሾማል፣ይሻራል፡፡
ሳቅና ጨዋታ ዝና ካማራችሁ
እንደኛ እንትን ላይ በተወለዳችሁ
የሚለው ዘፈናችንኮ ጤነኛ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳቅ፣ ጨዋታ እና ዝናን ለማግኘትአትችሉም እያለን ነው፡፡ ለምን ብንለው ከኛ ሀገር አልተወለዳችሁማ፤ ምን አማራጭአለን፡፡ መልሰን አንወለድ፡፡
ሌላ ቋንቋ ሲሰሙ ጆሯቸውን የሚያሳክካቸው፤ ፊታቸው የሚለዋወጥ፣ ንዴት ንዴት የሚላቸውእንዳሉ ሁሉ፤ ያንን ቋንቋ ሲሰሙ ቸርነታቸው ሁሉ የሚከፈት፣ መስተንግዷቸው የሚሟሟቅ፣አድሏዊነታቸው የሚጨምርም አሉ፡፡
የጎሳ ዘረኛነት ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ እና ለማግባባት ከምንሠራው ሥራይልቅ ልዩነታቸው እንዲገባቸው የምንሠራው ሥራ ይበልጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያን በመሰለችብዙ ቋንቋዎች በሚነገርባት ሀገር አንድ ተማሪ ከሥራ ቋንቋ ውጭ የራሱን አካባቢ ቋንቋ ብቻነው የሚማረው፡፡ ከዚያ ውጭ የሚማረው እንግሊዝኛ ነው፡፡ ከአካባቢው ቋንቋ ውጭ ያለውንየሚያስተምሩት መምህራንም አንዳንድ ጊዜ የጠላት ሀገር ቋንቋ የሚያስተምሩ ይመስል ወይ እነርሱ በግዴለሽነት  ያስተምራሉ አለያም አካባቢያቸው በንቀት ያያቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሕዝብ የሚናገራቸው ቋንቋዎች አሉ፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ሶማልኛን የመሰሉ፡፡ አንድ ተማሪ ከአካባቢው ቋንቋ በተጨማሪ ቢቻል ሌሎች ሁለትካልተቻለም አንድ የሌላ አካባቢ ቋንቋ መርጦ እንዲማር ቢደረግ እንዴት መልካም ነበር፡፡በመጀመርያ ደረጃ ጥላቻውን ያስቀረዋል፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር የመጥላት ሁኔታው ዝቅተኛነውና፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ያግባባናል፡፡ አንዳንዴኮ ከተወለድንበት እና ካደግንበት ክልል ውጭመሄድ ውጭ ሀገር እንደመሄድ እየሆነብን ነው?
አንድ የሶማሌ ሰው (6.0% ተናጋሪ አለው) አማርኛ (32.7% ተናጋሪ አለውእናኦሮምኛ (31.6% ተናጋሪ አለውቢችል ከስድሳ በመቶ በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያሕዝብ ጋር ይግባባል ማለት ነው፡፡ ይህም አንዱ ወደ ሌላው ሄዶ የመሥራት፣ ተጋብቶእና ተዋልዶ የመኖር ብሎም ከሌላው ወገኑ ጋር ልብ ለልብ የመግባባት ዕድሉንይጨምረዋል፡፡ እንግሊዝኛ በትምህርት ቤቶቻችን ያለውን ክብር ግማሽ ያህል የሀገራችንሌሎች ቋንቋዎች የላቸውም፡፡
ይህንን አመለካከት ቀርፈው ሕዝቡን ልዩነት ወደሚከበርበት አንድነት ያመጡታልየሚባሉት የፖለቲካ ልሂቃንም ራሳቸው ዘውገኞች ሆነዋል፡፡ አብዛኞቹ ፓርቲዎቻችንጎሳን ወይንም አካባቢን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ያንን ፓርቲ በአሠራሩ፣ በአመለካከቱእና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ብትወዱት እንኳን እንደገና እዚያ ክልል ገብታችሁ ለመወለድባለመቻላችሁ ብቻ ከአባልነት ትታቀባላችሁ፡፡
የሀገሬ ሰው «መወለድ ቋንቋ ነው» የሚለው እዚህ ላይ አይሠራም፡፡ መወለድ እኛ ሀገርቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ፓርቲም፣ ሥራም፣ ሹመትም፣ ገንዘብም፣ መሬትም፣ ርእዮተዓለምም ጭምር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አንድን ወገን ነጻ የሚያወጡ አያሌ ድርጅቶችአሉን በሀገራችን፡፡ ማን ማንን ከማን ይሆን ነጻ የሚያወጣው? አማራው ከትግሬው፣ትግሬው ከአማራው፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ አማራው ከኦሮሞው ነው ነጻ የሚወጣው?እየተጨቋቆንን ነው የምንኖረው ማለት ነው?
አንዳንዶቹ ፓርቲዎች እኛ ሕዝቡን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነው ነጻ የምናወጣውይላሉ፡፡ መቼም ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ መውጣትን የሚጠላ የለም፡፡ ግንከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ ለመውጣት የግድ ነጻ አውጭ ፓርቲ ያስፈልገናል?በዓለም ላይ ራሳቸውን ከድህነት አረንቋ ያወጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በነጻአውጭ ፓርቲዎች ነው እንዴ ነጻ የወጡት?
ፓርቲዎቻችን የጎሳ ዘረኛነትን ብቻ አይደለም የፓርቲ ዘረኛነትንም መላቀቅ አልቻሉም፡፡ከራሴ ፓርቲ አባል ውጭ ያለው ሁሉ ስሑት፣ ፀረ ልማት፣ ጨቋኝ፣ አንድነትንየሚያናጋ፣ አገር አጥፊ፣ ጠላት፣ ከሀዲ፣ ለሀገር የማይጠቅም ነው ብሎ ማሰብ ነውየፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ ብቻ ማድነቅ፣ መውደድ፣ መሾም እናማግነን ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ መጥላት፣ ማነወር፣ ማራቅ እናማግለል ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡
በርግጥ በአሁኑ ጊዜ በሕዝባችን ዘንድ ሰውን ብቻውን ማየት ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ሰው በቡድን ውስጥ ነው የሚታሰበው፡፡ በፓርቲው፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣ በክልሉ፣በሚኖርበት አካባቢ፣ በሥራ ዓይነቱ፣ ነው የሚታየው፡፡ እገሌ ሳይሆን እነ እገሌየሚለው ድምፅ ነው የሚሰማው፡፡
ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊውን የሚሰብኩት፣ ፍቅር እና ሰላም ዋና አጀንዳዎቻቸውየሆኑት የእምነት ተቋማት እንኳን ሳይቀሩ በዘረኛነት አረንቋ ውስጥ ሰምጠውበታል፡፡በአንድ በኩል የእምነት ዘረኛነት በሌላ በኩል ደግሞ የጎሳ ዘረኛነት እያላጋቸው ነው፡፡
አንድ ሰው በንግዱ፣ በአገልግሎቱ እና በሞያው መመረጥ ያለበት ባለው ችሎታ፣ ዐቅምእና ጥራት መሆን ነበረበት፡፡ አሁን አሁን ግን የኛው እምነት ሰው መሆኑ የበለጠ ቦታእየተሰጠው መጥቷል፡፡ ሙስሊሙ ሙስሊሙን ነጋዴ፣ ክርስቲያኑም ክርስቲያኑን ነጋዴእንዲመርጡ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች እየወጡ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው የንግድ እናየአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በሃይማኖታቸው ዘውግ ብቻ ከፍለው ከእነዚህ ብትገዛይመረጣል እያሉን ነው፡፡ ገንዘባችን በየእምነታችን እንዲሆን እየተሰበክን ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ ጥራቱ እንዴት ነው? የሚለው ቀርቶ ሙስሊም ነው የከፈተው ወይስክርስቲያን? ኦርቶዶክስ ነው የከፈተው ወይስ ፕሮቴስታንት ሆኗል ጥያቄው፡፡ መርፌውንበየእምነታችን ሊወጉን የተዘጋጁ የሕክምና ተቋማትም ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በአንዳንድመሥሪያ ቤቶች ለመቀጠር የአንድ እምነት ተከታይ መሆን ብቻ ከትምህርትም፣ከልምድም በላይ ዋጋ ሲኖረው እያየን ከመገረም አልፈን ለምደነዋል፡፡
የእምነት ተቋማቱ ከዚህም አልፈው የጎሳውን ዘረኛነት የሚያባብሱ ተቋማትም ሆነዋል፡፡ጎጃሜ ጎጃሜውን፣ ጎንደሬ ጎንደሬውን፣ ትግሬ፣ ትግሬውን፤ ኦሮሞ ኦሮሞውን፣ ወሎወሎዬውን ሲስበው ማየት ለተቋማቱ ቅርብ ለሆነው ብቻ ሳይሆን ርቆ ላለውምእመናቸውም የዕለት ዜና ሆኖለታል፡፡ የአንደኛው ወገን በእምነት ተቋማቱ የሥልጣንእርከን በወጣ ቁጥር፣ የእምነቱን ተከታዮች ከማብዛት ይልቅ የወንዙን ልጆች ማብዛትዋናው ተልዕኮው እየሆነ ነው፡፡
መካ ላይ አላሁ አኩበር ያለው ቢላል ኢትዮጵያዊ እንጂ ሳዑዲያዊ አለመሆኑ ተረስቷል፡፡ደብረ ዳሞ ላይ የሚከብሩት አቡነ አረጋዊ የአውሮፓ ሰው እንጂ ኢትዮጵያዊእንዳልነበሩ ተዘንግተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብለውየሚያስተናግዱበት፣ በእምነቱ ከመሰላቸው ሀገራቸውን ሀገሩ አድርገው የሚሰጡበት ዘመንእንዳይቀር ያሰጋል፡፡
ስንቶች ከሌላ ክልል ብቻ ሳይሆን ከሌላ ሀገር መጥተው፣ ትውልዳቸውንም ረስተውኢትዮጵያውያን ሆነው ቀርተዋል፡፡ «እኔስ በሀገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ» ነበርየምንለው፡፡ ዛሬ ይሄ ተረት ሊሆን ነው መሰለኝ፡፡ አቡነ አረጋዊን ትግሬ፣ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስንም አማራ አድርጎ የሚያይ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ሁለቱም ግን እንኳንእና ትግሬ እና አማራ ኢትዮጵያዊም አይደሉ፡፡
ልጁ ሊቀጠር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል፡፡ ታድያ መካሪዎች «ስትሄድ ጳጳሱየሀገራቸውን ሰው ይቀጥራሉና ሀገርህ የት ነው ካሉህ ያንተን አትናገር የርሳቸውን ሀገርተናገር» ብለው ይነግሩታል፡፡ ታድያ ጳጳሱ ፊት ሲቀርብ የሀገራቸው ስም ጠፋው አሉ፡፡
እንደገባ  የተነገረው አልቀረም
«ሀገርህ የት ነው አሉት
«የርስዎ ሀገር» አላቸው፡፡
«የኔ ሀገር የት ነው አሉት
«ከኔ ሀገር» አላቸው አሉ፡፡ ምን ያድርገው፡፡
አንዳንዶችማ ከዚህም ወርደው ወርደው የቆብ ዘረኛነትም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሕጋውያንካህናት ከታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪነት እንዲወገዱ ዐዋጅ ያወጣው ማን ይሆን? ዛሬለሹመት ዋና መመዘኛው መመንኮስ ሆነና «መነኮሰ ሞተ» የሚለው ትርጓሜ «መነኮሰበላ» ወደሚለው ዞረ፡፡ በዚህ የቆብ ዘረኛነት ምክንያትም መመንኮስ የሌለባቸው ለሥራእና ለሹመት ሲሉ እንዲመነኩሱ አንዳንዶችም ሚስቶቻቸውን ደብቀው እንዲመነኩሱአደረግናቸው፡፡ በተለይም የውጩ ሀገር ዕድል ሁሉ ከሕጋውያን ይልቅ ለመነኮሳቱ እጅግክፍት እየሆነ ሲመጣ፣ ያልገባቸው እና ያልተገባቸው መነኮሳት እየበዙ መጡ፡፡
ከዚህም አልፎ ምንኩስናዊ ሕይወቱ ሳይሆን የት መነኮሰ? የሚለው የዘረኛነት መለኪያእየሆነ ነው፡፡ እናም የት ብመነኩስ የምንኩስናን ተጋድሎ እፈጽማለሁ? መባሉ ቀርቶየት ብመነኩስ ቶሎ ሹመት አገኛለሁ? ሆነ ጥያቄው፡፡
«የኛ ልጆች» የሚሉ የማኅበርተኞችን የዘረኛነት ቋንቋስ ሰምታችሁ አታውቁም፡፡ ዛሬ ዛሬአያሌ ማኅበራት እየተፈጠሩ ነው፡፡ የሃይማኖት፣ የጉዞ፣ የሞያ፣ የበጎ አድራጎት፣ የክብካቤ፣የሌሎችም ማኅበራት፡፡ አንድን ሥራ ለማከናወን አንድነት መፍጠሩ መልካም ሆኖ ሳለዘረኛነቱ ግን ከፋ፡፡ «እንዲህ ሲል ያውካል» አለ ተርጓሚ፡፡ የሰውን ስሕተተኛነት እናትክክለኛነት ከማኅበራቸው አባልነት አንፃር ብቻ የሚተነትኑ ማኅበርተኞች አሉ፡፡
ይህን የመሰለ ቁመና ይዘሽ
ምናለ ፈጣሪ የኛ ባረገሽ
የሚለው ሀገርኛ ዘፈን ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡
ምን መልካም ብትሠሩ፣ ምን ተአምር ብትፈጽሙ እነርሱ ከገቡበት ካልገባችሁ ሥራችሁሁሉ የመርገም ጨርቅ ይሆናል፡፡ ምን ተሠራ? ሳይሆን ማን ሠራው? ነው ለእነርሱቁም ነገሩ፡፡ በማኅበር ይወዳሉ፣ በማኅበር ይጠላሉ፣ በማኅበር ያቀርባሉ፣ በማኅበርያገላሉ፣ በማኅበር ያጸድቃሉ፣ በማኅበር ይኮንናሉ፣ በማኅበር ይረዳሉ፣ በማኅበርይነፍጋሉ፡፡ አባል ከሆናችሁ ሁለት እና ሁለት አምስት ይሆንላችኋል፤ አባል ካልሆናችሁግን እንኳን አምስት አራት አይሆንላችሁም፡፡
በጎ ነገር ስትሠሩ ካዩዋችሁ ሊያበረታቷችሁ እና ሊያግዟችሁ አይደለም የሚፈልጉት፤ሊያደንቋችሁ እና ሊያመሰግኗችሁ አይደለም የሚተጉት፤ አባል ሊያደርጓችሁ እንጂ፡፡ምክንያቱም ከማኅበራቸው ውጭ በጎ ነገር ሲሠራ ማየት ስለማይፈልጉ፡፡
ዘረኛነት የሁላችንም ጠባይ እየሆነ ነው፡፡ ከጎሳው ብናመልጥ፣ ከፓርቲው፣ ከፓርቲውብናመልጥ ከእምነቱ፣ ከእምነቱ ብናመልጥ ከማኅበሩ ጎጠኛነት ውስጥ መገኘታችንአልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ ሰዎች በሥራቸው፣ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በችሎታቸው፣በዐቅማቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በትጋታቸው እና በጥረታቸው ሳይሆን በአንዳችወገንተኛነታቸው እንዲመዘኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ወልጋዳ ሚዛን ደግሞ ወዳጆችንእንጂ ጎበዞችን፣ ወገንተኞችን እንጂ ሊቆችን ዕድል አይሰጥም፡፡
አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆችእንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህልተሰባስበን አልነበር?
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! አሜን።